Jeremiah 41

1ከንጉሣዊ ቤተ ሰብ የሆነው ከንጉሡ የጦር መኰንንኖች አንዱ የነበረው የኤሊሳማ ልጅ የናታንያ ልጅ እስማኤል፣ በሰባተኛው ወር ከዐሥር ሰዎች ጋር ወደ ምጽጳ ወደ አኪቃም ልጅ ወደ ጎዶልያስ መጣ፤ በዚያም በአንድነት ሊበሉ በማእድ ተቀምጠው ሳለ፣ 2የናታንያ ልጅ እስማኤልና አብረውት የነበሩ ዐሥሩ ሰዎች ተነሥተው፣ የባቢሎን ንጉሥ በምድሪቱ ላይ ገዥ አድርጎ የሾመውን የሳፋንን ልጅ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በሰይፍ መቱት፤ ገደሉትም። 3ደግሞም እስማኤል በምጽጳ ከጎዶልያስ ጋር የነበሩትን አይሁድ ሁሉ፣ በዚያም የተገኙትን የባቢሎን
ወይም የከለዳውያን
ወታደሮች ገደላቸው።

4ጎዶልያስ በተገደለ ማግስት፣ ማንም ስለ ሁኔታው ከማወቁ በፊት፣ 5ሰማንያ ሰዎች ጢማቸውን ተላጭተው፣ ልብሳቸውን ቀድደው፣ ገላቸውን ነጭተው የእህል ቍርባንና ዕጣን በመያዝ ከሴኬም፣ ከሴሎና ከሰማርያ ወደ እግዚአብሔር ቤት ለማቅረብ መጡ። 6የናታንያ ልጅ እስማኤል ሊገናኛቸው እያለቀሰ ከምጽጳ ወጣ፤ ሲያገኛቸውም፣ “ወደ አኪቃም ልጅ ወደ ጎዶልያስ ኑ” አላቸው። 7ወደ ከተማዪቱ በገቡ ጊዜ፣ የናታንያ ልጅ እስማኤልና አብረውት የነበሩ ሰዎች ዐረዷቸው፤ በውሃ ማጠራቀሚያ ጕድጓድ ውስጥም ጣሏቸው። 8ከተገደሉት ጋር የነበሩ ዐሥር ሰዎች ግን እስማኤልን፣ “እባክህ አትግደለን! በዕርሻችን ውስጥ የሸሸግነው ስንዴና ገብስ፣ የወይራ ዘይትና ማር ስላለን እባክህን አትግደለን” አሉት። እርሱም ተዋቸው፤ ከሌሎቹም ጋር አልገደላቸውም። 9እስማኤል ከጎዶልያስ በተጨማሪ የገደላቸው ሰዎች ሁሉ ሬሳ የተጣለበት የውሃ ማጠራቀሚያ ጕድጓድ፣ ንጉሡ አሳ የእስራኤልን ንጉሥ ባኦስን ስለ ፈራ ለመከላከል ያሠራው ነበር፤ ይህን ጕድጓድ የናታንያ ልጅ እስማኤል በሬሳ ሞላው።

10እስማኤል በምጽጳ የቀረውን ሕዝብ ሁሉ ምርኮኛ አደረገ፤ እነርሱም የባቢሎን የክብር ዘበኞች አዛዥ ናቡረዘረዳን የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በላያቸው ገዥ አድርጎ የሾመባቸው የንጉሡ ሴቶች ልጆችና በዚያ የቀሩት ሌሎች ሰዎች ሁሉ ነበሩ። የናታንያ ልጅ እስማኤል እነዚህን ማርኮ ወደ አሞናውያን ለመሻገር ተነሣ።

11የቃሬያ ልጅ ዮሐናና ከእርሱ ጋር የነበሩት የጦር መኰንኖች ሁሉ የናታንያ ልጅ እስማኤል የፈጸመውን ግፍ ሁሉ በሰሙ ጊዜ፣ 12የናታንያን ልጅ እስማኤልን ሊወጉ ሰዎቻቸውን ሁሉ ይዘው ሄዱ፤ በገባዖንም ባለው በታላቁ ኵሬ አጠገብ ደረሱበት። 13እስማኤል የያዛቸው ሰዎች ሁሉ የቃሬያን ልጅ ዮሐናንንና አብረውት የነበሩትን የጦር መኰንኖች ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው። 14እስማኤል ከምጽጳ ማርኮ የወሰዳቸው ሰዎች ሁሉ አምልጠው ወደ ቃሬያ ልጅ ወደ ዮሐናን ገቡ። 15የናታንያ ልጅ እስማኤል ግን አብረውት ከነበሩት ስምንት ሰዎች ጋር ከዮሐናን አመለጠ፤ ሸሽቶም ወደ አሞናውያን ገባ።

ሽሽት ወደ ግብፅ

16የቃሬያ ልጅ ዮሐናንና ከእርሱ ጋር የነበሩት የጦር መኰንንኖች ሁሉ የናታንያ ልጅ እስማኤል የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን ከገደለ በኋላ፣ በምጽጳ ከማረካቸው የተረፉትን ሰዎች በማስመለስ ይዘው ሄዱ፤ እነዚህም፣ ወታደሮች፣ ሴቶች ሕፃናትና ከገባዖን ያመጧቸው የቤተ መንግሥት ባለ ሥልጣኖች ነበሩ። 17ከዚያም ተነሥተው ሄዱ፤ ወደ ግብፅም በማምራት በቤተ ልሔም አጠገብ ባለችው በጌሮት ከመዓም ዐረፉ፤ 18ወደ ግብፅም የሄዱት ከባቢሎናውያን
ወይም ከከለዳውያን
ለማምለጥ ነበር፤ ባቢሎናውያንንም የፈሩት የናታንያ ልጅ እስማኤል የባቢሎን ንጉሥ የምድሪቱ ገዥ አድርጎ የሾመውን የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በመግደሉ ነው።

Copyright information for AmhNASV